የሚሊኒየሙ የችግኝ ተከላ ፕሮጀክት ውጤታማ መሆን ድህነትን ማስወገድ እንደሚቻል የሚያመለክት መሆኑን የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ገለጹ
ባህር ዳር ነሐሴ 21 ቀን 1999 - በአማራ ክልል በተካሄደው የ2 ዛፍ ለ2 ሺህ የችግኝ ተከላ ፕሮጀክት የተመዘገበው ውጤት ሀገሪቱ የምትታወቅበትን ድህነት በአዲሱ ሚሌኒየም ማስወገድና ታሪክ ማድረግ እንደሚቻል የሚያመለክት መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አስታወቁ። በፕሮጀክቱ 54 ሚሊዮን ችግኞች ተተክለዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ አያሌው ጎበዜ የክልሉ ሚሌኒየም በዓል አከባበር ምክር ቤት ሶስተኛ መደበኛ ጉባኤ ዛሬ በባህርዳር ከተማ ሲጀመር ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ወደ ሶስተኛው ሚሌኒየም ለመሸጋገር የታደለው የአሁኑ ትውልድ በአዲስ አስተሳሰብና የስራ መንፈስ ድህነትን ታሪክ የማድረግ ኃላፊነት ተጥሎበታል ብለዋል።
የታሪክ አጋጣሚ የፈጠረውን ይህን ሀገራዊ ኃላፊነት ለመወጣት የአማራ ክልል የሚሌኒየም በዓል አከባበር ምክር ቤት የክልሉን ህዝብ የሚያሳትፉ የልማት ፕሮጀክቶችን አጽድቆ ተግባራዊ ለማድረግ ሲንቀሳቀስ መቆየቱን ገልጸዋል።
በተለይ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተዘጋጀውን የችግኝ ተከላ ፕሮጀክት ተግባራዊ ማድረግ በምክር ቤቱ ትኩረት ተሰጥቶት ሲከናወን መቆየቱን የተናገሩት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ በዚህም አጥጋቢ ውጤት መገኘቱን አመልክተዋል።
በክልሉ ህዝብ ከፍተኛ ተሳትፎ የተካሄደው የችግኝ ተከላ መርሀ ግብር ውጤታማ መሆኑ ደግሞ ሀገሪቱ የምትታወቅበትን ድህነትና ላቀርነት ታሪክ ለማድረግ ረጅም ጊዜ እንደማይወስድ የሚያሳይ መሆኑን አቶ አያሌው አስታውቀዋል።
የክልሉ ህዝብ ለዘመናት ይዞት የቆየውን የመቻቻል ባህል አጎልብቶና እጅ ለእጅ ተያይዞ በአዲሱ ሚሌኒየም አዲስ ታሪክ ለመስራት በመዘጋጀት የሽግግር በዓሉን እንዲያከብርም ጥሪ አቅርበዋል።
የክልሉ ሚሌኒዬም በዓል አከባበር ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው አሊ ለምክር ቤቱ ባቀረቡት ሪፖርት በክልሉ በተካሄደው እንቅስቃሴ በዕቅድ ከተያዘው በላይ 54 ሚሊዮን ሀገር በቀል የዛፍ ችግኞች መተከላቸውን ጠቁመዋል።
ህብረተሰቡ ችግኞችን በመትከል ያሳየውን ተሳትፎ የተተከሉትን በመጠበቅና በመንከባከብ ለመድገም ገንዘብ አዋጥቶ ዘበኛ በመቅጠር ጭምር ችግኞችን እየጠበቀ መሆኑን አስረድተዋል።
ከዚህም ሌላ ጽህፈት ቤቱ ባዘጋጀው የዘመን ሽግግር ዋዜማና ማግስት የበዓል አከባበር ፕሮግራም መሰረት ለሚቀጥሉት ስድስት ሳምንታት የህጻናት ስፖርትና የኪነ ጥበብ ፌስቲቫል፣ የእግር ጉዞ፣ የሙዚቃ ዝግጅትና የስዕል ኤግዚቢሽን፣ የችቦ ማብራትና የርችት ስነ ስርዓት እንደሚከናወን አስታውቀዋል።
ለሁለት ቀናት በሚካሄደው በዚሁ ጉባኤ ላይ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ሽታዬ ምናለ፣ የኢትዮጵያ ሚሌኒዬም በዓል አከባበር ጽህፈት ቤት ዋና ዳሬክተር አቶ ስዩም በረደድና ታዋቂ አርቲስቶች ተገኝተዋል።
የጉባኤው አባላት በነገው ዕለት የአባይ ሚሌኒየም ፓርክን መርቀው እንደሚከፍቱ እንዲሁም ለሚሌኒየሙ በዓል የተቋቋመው የክልሉ የባህል ቡድን ስራ እንደሚጀምር ከወጣው መርሃ ግብር ለመረዳት ተችሏል።
|