በለንደን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የሚሌኒየሙን ለማክበር በዝግጅት ላይ ናቸው
አዲስ አበባ ነሐሴ 21 ቀን 1999 - በለንደንና በመላው ዓለም የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የሚሌኒየሙን በዓል በደማቅ ሁኔታ ለማክበር በዝግጅት ላይ መሆናቸውን የለንደን ፍሪ ፕሬስ ዘገበ፡፡
ማንም ሰው ሁለት ሺህ ዓመትን ሲያከብር የሚሰማው ዓይነት ደስታ ተሰምቶኛል፡፡ ይህ ለኛ ልዩ አጋጣሚ ነው ብላለች በለንደን የእናት ሬስቶራንት ባለቤት ድንቅነሽ ስመኝ፡፡ በዓሉን በኢትዮጵያ ለማክበር ባለመቻሏ እንዳዘነችም ድንቀነሽ ገልጻለች፡፡
ሚሌኒየሙን ለማክበር ከ40 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያንና የሌሎች አገር ዜጎች ወደአገር ውስጥ ይገባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ዘገባው አመልክቷል፡፡
ኢትዮጵያ የበርካታ ባህሎች ባለቤት ናት ያለችው ድንቅነሽ በዓሉን ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች ያከብሩታል ብላለች፡፡
ለበዓሉ ፓርቲ እንደምታዘጋጅና በዝግጅቱ ላይም የኢትዮጵያ ባህላዊ ምግቦችና መጠጦች እንደሚቀርቡ ገልጻለች፡፡
የኢትዮጵያ ሚሌኒየም በዓል አከባበር ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ዳይሬክተር ስዩም በረደድ በበኩላቸው በዓሉ አገሪቱ ያላትን ከፍተኛ ቅርስ የምትዘክርበትና ትክክለኛ ገጽታዋን የምታሳይበት ነው ብለዋል፡፡
ሚሌኒየሙ ኢትዮጵያ ቀድሞ ትታወቅባቸው የነበሩትን በጎ ያልሆኑ ነገሮች ለመቀየር ትልቅ እድል የሚፈጥር አጋጣሚ ነው ብለዋል፡፡ |